የእርሻ ስነ-ቃል (ገበሬን የሚያወድሱ)

የስነ-ቃል አይነቶች የተለያዩ ቢሆኑም ለዛሬ ክረምት መግቱን ተከትሎ

የአገራችን ገበሬ በእርሻው ዙሪያ በሬውን የ ሚያሞግስበትን አጫጭር ግጥማዊ ስነ-ቃሎች ላካፍላችሁ፡፡

 

ገበሬ በሬውን የሚጠራበት እሞች ብዙ ናቸው  አንዱን ለማንሳት ያክል «ጎኔ» በማለት

ጎኔ ማለት አንዱ የሰውነቴ ክፍል ነህ እንደማለት ነው፡ 

በሬ ቢታመምበት ወይም የሆነ ነገር ቢሆንበት አንዱ የሰውነቱ ክፍል የታመመ ያህል ነው የሚሰማው፡

 

በርዬ አንተን ያጡ
ጎንዬ አንተን ያጡ
አተላ ጨለጡ
ማህበር ቀላወጡ
እያሏቸው መጡ።

ገበሬ የበሬውን ውለታ በማመስገን ይገልጻል።

በሬውን እንደ ሕፃን ልጅ «እሹሩሩ» ብሎ የማዘል ያህል ነው የሚንከባከበው።በስራ ወቅት ደግሞ አውድማ ውስጥ እንዲህ ይለዋል።

እሹሩሩ ጎኔ
እሹሩሩ ጎኔ
የበሬን ውለታ እንጫወት ማታ
እየበላን ንፍሮ በሰፊ ገበታ።

እኔ አልገዛም ክላሽ ጦሱ ይተርፈኛል
እኔ አልገዛም በቅሎ ፈሷ ይገማኛል
የበርዬ ትንፋሽ ሸታው ደስ ይለኛል።

ሰነፍ ገበሬ ገንዘቡን ከበሬ መግዣነት ይልቅ ለሌላ ጥፋት ስለሚያውል ከጓደኞቹ በታችይሆናል እህል ሊበደር ከታታሪገበሬ ደጅ ይጠናል። ለእንዲህ ዓይነቱ ሰው ነው ገበሬው እንዲህ ያለ


በሬ አንተን የጠላ ጎኔ አንተን የጠላ
የገና የጥምቀት ይለምናል ጠላ።
ምነው በቅዳሜ ምነው በእሑድ ቢያርሱ
ከባለ ፀጋ ቤት ከሚመላለሱ።

ገበሬው በሆነ አጋጣሚ በሬውን ቢያጣ አንድ አካሉ እንደጎደለ ነው የሚቆጥረው በጣም ይደነግጣል ለዚህም ነው እንዲህ የሚለው፡


በርዬ አንተን አልባ
ጎንዬ አንተን አልባ
አይኔም አያይልኝ
ጆሮዬም አይሰማ
!

የበሬ የሥራ ትጋት ከሰዎችም ሆነ ከሌሎች የቤት እንስሳት ይበልጣል ለዚህም ነው ገበሬው አብዝቶ የሚያወድሰው በእርሻ ወቅት ያርሳል፤ በእንዲህ ዓይነቱ የመኸር ወቅት ደግሞ ያበራያል ለዚህ ውለታውም እንዲህ እያለ ያወድሰዋል

በሬ እንደ አንተ የሚሆን የሚሸከረከር
ጎኔ እንደ አንተ የሚሆን የሚሽከረከር
እንዝርትም አይገኝ ከፈታይ መንደር።
   በርየ ሲሰራ ጎንየ ሲሰራ
   ይመስላል ደብተራ

  ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቅኔ የሚመራ

በግብርና ሥራ ውስጥ ሌሎች የቤት እንስሳትም ሚና አላቸው ለምሳሌ የተወቃውን እህል በሸክም ወደቤት

የሚያደርሱት የጋማ ከብቶች ናቸው፡ እዚህ ላይ ታዲያ ከፍተኛውን ሚና የተወጣው በሬ ይረሳና ፈረሶች ይመሰገናሉ፡

ምክንያቱም የመጨረሻውን ምርት ተሸክመው ስለሚመጡ ነው በዋናነት የሚፈለገው ደግሞ ምርቱ ነው

ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ገበሬው የበሬውን ውለታ አይረሳም፡ አንተ ባታርሰው ኖሮ፣ አንተ ባታበራየው ኖሮ ፈረሱ

ከየት የመጣ ምርት ነው የሚሸከም በማለት ይመስላል እንዲህ ይላል

የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ
ከኋላ ተነስቶ ከፊት በመድረሱ

 

ገበሬውን ከእርሻው አይለይብን!